|
Est. 2010 we can not direct the wind but, we can adjust the sails. |
| news.. |
|
የሲድኒ የመረዳጃ እድር የመጀመሪያውን ጠቅላላ ስብሰባ አካሄደ (also in pdf) ኖቬምበር 7 እሑድ በሊድከም አዳራሽ የእድር ምስረታን አስመልክቶ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችና የተመዘገቡ የእድሩ አባላት በተገኙበት ስብሰባ ተካሂዷል። እድሩን በማሰባሰብና እስከአሁንም ስራውን ሲያካሂድ የቆየው የግዚያዊ ኮሚቴ ም/ዳኛ የሆኑት አቶ እስማኤል ሱሊማን ሕዝቡን አመስግነው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “የምንኖረው በሰው ሀገር ሲሆን አብዛኛው ሕብረተሰባችን ግን የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለማቃናት ደፋ ቀና ከማለት አልፎ የመኖርን ያህል መሞትም እንዳለ የተገነዘበው አይመስልም” ብለዋል። በዚህ አይነት ሁኔታ መቀጠልም ማብቃት ያለብት ጉዳይ እንደሆነም አስገንዝበዋል። ስለሆነም ብቸኛው አማራጭ የተመሰረተውን እድር በመደጋገፍ ማራመድና ማሳደግ የሁላችንም የትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል። በመጋቢት ወር 2010 አጋማሽ ላይ ከተለያየ አካባቢና የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ 14 የስድኒ ነዋሪዎች ስብሰባ አድርገው እድር ለመመስረት ሁኔታዎችን አመቻቹ። ቀዳሚ ተግባር አድርገው የተነሱት አላማውንና ለአባላት የሚሰጠውን አገልግሎት በዝርዝር የያዘ መተዳደሪያ ደንብ ማርቀቅ ነበር። የእድሩ ፀሃፊ አቶ ስሎሞን ከበደ ዓላማዎቹን እንደሚከተለው ገልጸዋል፤ 1. በአባል ላይ ሐዘን ሲደርስ የችግሩ ተካፋይ በመሆን መተጋገዝ። ይህም የተመደበውን የገንዘብ መጠን መሰጠት እና ከቀብር ስርዓቱ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ስራዎችን በመስራት አገልግሎት መስጠት። 2. አንድ አባል ወይም የቤተሰቡ አባል ቢታመም ቤተሰቡ በሚፈቅደው መንገድ በመጠያየቅ መተጋገዝ። 3. የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ አባላትና ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲቀራረቡና እንዲጠያየቁ አጋጣሚዎችን መፍጠር። የሚሉት ሲሆኑ መርዶን በተመለከተ ግን እድሩ ምንም ዓይነት የገንዘብ ወይም ሌላ አገልግሎት እንደማይሰጥ ጠቁመዋል። ፀሃፊው በመቀጠልም አባላት ከእድሩ የሚያገኙት ጠቀሜታ፣ የአባላት መብትና ግዴታ በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ የሰፈሩትን አንቀጾች በማንበብ አብራርተዋል። የፋይናንስ ሪፖርትና የተዘረጋውን ግልጽ የአሰራር ዘዴ በተመለከተ ገንዘብ ያዥና የፋይናንስ ኃላፊዎቹ አቶ ለማ ብሩና አቶ ግርማ ፈይሳ በቅደም ተከተል ገለጻ አድርገዋል። በመተዳደሪያ ደንቡ እንደሰፈረውም የፋይናንስ ሪፖርት ማለትም ወጪና ገቢ እንዲሁም በየወቅቱ ያለው የእድሩ ካፒታል በጥሬ ገንዘብና ንብረት ለአባላቱ በደብዳቤ/በኢሜል የገለጻል። ከዚያም ከአባላት በቀረቡ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል። በዕለቱም ወ/ሮ ውብዓለም ያሊ ከእድሩ የምስረታ ስብሰባ ጋር ተስማሚ የሆነ ግጥም በማቅረብ ተስብሳቢውን አዝናንተዋል። በታደለው ፕሮግራም መሰረት ሌላው የመነጋገሪያ አጅንዳ የነበረው የኮሚቴ አባላትን ምርጫ ማካሄድ ነበር። አሁን ያለው ኮሚቴ ግዚያዊ በመሆኑ እድሩ ደግሞ በግዚያዊ ኮሚቴ መቀጠል ስለማያስፈልገው ቋሚ ኮሚቴና የመካሪ ጉባኤ አባላት እንዲመረጡ የስብሰባው መሪ አጀንዳውን ከፍተዋል። ብዙ ሰዎ እጃቸውን በማንሳት ያለው ኮሚቴ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲያገልግልና የጀመሯቸውን ስራዎች ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል ተብሏል። በሌላ በኩልም የኮሚቴ አባላቱ ስብጥር ኅብረተስቡን በሰፊው የሚወክል ሆኖ ስለሚታይ በዚሁ ይቀጥሉ የሚሉና ተመሳሳይ ድጋፎች ተሰንዝረዋል። ያሉት 8 የኮሚቴ አባላት እንዳሉ ሆነው በነሱ ላይ ሁለት አባላት እንዲጨመሩ በተወሰነው መሰረት ወ/ሮ ዓይናለም ተስፋዪና አቶ ሲሳይ ካሴ በአንድ ድምጽ ተመርጠዋል። ስብሰባው ከመጠናቀቁ በፊትም የእድሩ ዳኛ አቶ ፍቅሩ አበራ የማጠቃለያ ንግግር እንድያደርጉ አቶ እስማአኤል ጋብዘዋል። በአካላቸው ላይ በደረሰው ጉዳት ለጊዜው በማገገም ላይ እንድሚገኙ ገልጸዋል። የእድርን አስፈላጊነት በተለይም ለረጅም ግዜ ሲታሰብ የቆየው የእድር ምስረታ ሃሳብ በተግባር ከግብ ሊደርስ የመቻሉን አድማስ ማየት ለሁላችንም ከፍተኛ ደስታን የሚሰጥ ነው ብለዋል። ዛሬ የተሰጠንን የህዝብ አስተያየት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ኃላፊነታችንን ለመወጣት የቻልነውን እንሰራለን በማለት ገልጸዋል። ሁላችንም ከተባበርን እድሩን ለከፍተኛ ቦታ ማድረስ ሊከብደን አይችልም በማለት የህዝቡን ተሳትፎ አድንቀው ዝግጅቱ በዚሁ ተጠናቋል። |
| contact us: P. O. Box 279 Auburn NSW 1835 Tel. 0434 287 709; 0404 458 158 ethiopianidir@gmail.com bank details: Commonwealth Bank (Blacktown) BSB No. 062339 Acc. No. 10548769 |
| Ethiopian Cooperative IDIR in Sydney; IBN: 'on process'; Registered Licence No.: 'on process'; November 2010 |